ጥቅምት 22 ቀን 2016 ዓ.ም (አንካራ)
በቱርኪዬ የኢፌዲሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር እና ልዬ መልዕክተኛ ክቡር አምባሳደር አደም መሐመድ የTurks Abroad and Related Communities (YTB) ፕሬዝደንት ከሆኑት Mr. Abdullah Eren ጋር በነጻ የትምህርት ዕድል ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል።
ክቡር አምባሳደር አደም ኢትዮጵያ የአስር ዓመት የልማት ዕቅድ ነድፋ እየተንቀሳቀሰች መሆኗን በማብራራት ይህን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ ጉልህ ሚና የሚጫወተውን የትምህርት ዘርፍ ይበልጥ ለማሻሻል ልዬ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ገልጸዋል።
ክቡር አምባሳደር አደም ቱርኪዬ የከፍተኛ ትምህርትን በተመለከተ በዓለምአቀፍ ደረጃ የተሻለ ልምድ ካላቸው አገራት ተርታ የምትመደብ መሆኗን ጠቅሰው አገሪቱ ለኢትዮጵያ ተማሪዎች እንዲሁም ለከፍተኛ ት/ርት መምህራን የምትሰጠውን የነጻ ትምህርት ዕድል አጠናክራ እንድትቀጥል የጠየቁ ሲሆን፣ የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር ለሚስዮናችን በላከው ለከፍተኛ ት/ርት መምህራን የነጻ ት/ርት ዕድል እንድናፈላልግ በሚጠይቀው ደብዳቤ ዙሪያ ከፕሬዝደንቱ ጋር ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጓል።
የYTB ፕሬዝደንት በበኩላቸው ቱርኪዬ ከኢትዮጵያ ጋር የቆዬ ወዳጅነት ያላት አገር መሆኗን ገልጸው የቱርኪዬ መንግስት ለኢትዮጵያ ተማሪዎች የነጻ ከፍተኛ ት/ርት ዕድል እየሰጠ እንደሚገኝ እና ወደፊትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያብራሩ ሲሆን፣ ከኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር ለሚስዮናችን የተላከውን ደብዳቤ በተመለከተ ተቋማቸው በአዎንታ እንደሚመለከተው ገልጸዋል።
የቱርኪዬ መንግስት የሚሰጠውን የነጻ ትምህርት ዕድል አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በትብብር መስራት እንደሚፈልግ የገለጹት ፕሬዝደንቱ፣ ይህን ትብብር በአገራችን በሚገኙ ሌሎች ሚኒስቴር መ/ቤቶች ለማስፋፋት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
YTB በቱርኪዬ መንግስት የሚደገፍ የዓለምአቀፍ ተማሪዎችን የነጻ ት/ርት ዕድል እየሰጠ የሚገኝ ተቋም ሲሆን፣ 265 የሚሆኑ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ተቋሙ በሚሰጠው የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ማስተርስ ዲግሪና PhD ዲግሪ የነጻ ት/ርት ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።

Disclaimer: The official text of the Embassy Website is the English language version. Any discrepancies or differences created in translations are not binding and have no legal effect for compliance or enforcement purposes.

X
Twitter
Facebook
YouTube
Instagram